የመንግሥትን የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለማዘመንና አሰራሩን ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ የዘመናዊ ዲጂታል የንብረት አስተዳደር ሥርዓት (PMS Software System) ይፋዊ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሄደ።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ያህያ የክልሉ መንግሥት በንብረት አስተዳደር ሂደት ላይ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችንና መንስኤዎቻቸውን በዝርዝር በመለየት፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን ገልጸዋል።
ቢሮ ኃላፊው አክለውም በአሁኑ ወቅት ዲጂታላይዜሽን ለመንግሥት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው አቅጣጫዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሁሉም የመንግሥት ንብረቶች መረጃ በአንድ ማዕከላዊ ዲጂታል መዝገብ (Database) ስር እንዲካተት ማድረግ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል።
ቢሮ ሀላፊው አጠቃለው ሲናገሩ ሁላችንም የተሰጠንን ኃላፊነት በጥራት በመወጣት እና አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት በማጠናቀቅ የዚህ ዘመናዊ ሥርዓት ስኬታማ ትግበራ አካል እንድንሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ በማለት ሥርዓቱን በይፋ አስጀምረዋል።
በመድረኩ ላይ ስለ ዘመናዊ ዲጂታል የንብረት አስተዳደር ሥርዓቱ (PMS) በባለሙያዎች ዝርዝር የቴክኒክ ገለጻ የቀረበ ሲሆን በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ እብደራሂም በሰጡት እቅጣጫ ለማስጀመር የተለዩት መሥሪያ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች መሥሪያ ቤቶችም ወደ ዲጂታል አሰራር ለመግባት የሚያስፈልገውን ቅድመ-ዝግጅት በፍጥነት እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የመንግሥት ሀብትን በአግባቡ ለማስተዳደር ለሚደረገው ጥረት የሴክተር መሥሪያ ቤት እና የወረዳ መስተዳድር ኃላፊዎች በባለቤትነት ስሜት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተሳታፊዎች ላሳዩት ንቁ ተሳትፎ እና ላነሷቸው ጠቃሚ ሐሳቦች ምስጋና አቅርበው፣ በቀጣይም ተከታታይነት ያለው ስልጠና እንደሚሰጥ በመግለጽ የመድረኩን ፍጻሜ አብስረዋል።
በዚህ የይፋዊ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ የወረዳ መስተዳድሮች እና በየደረጃው የሚገኙ የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።
ሐምሌ 28/2018

















